ማህበራዊ ፕሮግራም

የማኅበራዊ ፕሮግራም ዓላማ፡- ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ አካታች ማኅበራዊ ልማት

ሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት መነሻዋ ዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ ሁለንተናዊ ማኅበራዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዳይ የፓርቲያችን የማኅበራዊ ፕሮግራም አንድ ዋና ትኩረት ይሆናል። በመሆኑም የማኅበራዊ ልማት ሥራዎቻችን የዕድገትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መንትያ ግቦችን የማሳካት ጉዳይ ይሆናል። ማኅበራዊ የልማት ሥራዎቻችን ከችሮታና ከነባሩ የማኅበራዊ ደኅንነት ትኩረት ወጥቶ ችግሩን ከመብት አንፃር የሚመለከተው ይሆናል። የማኅበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተደራሽነትና አካታችነት ባለው መልኩ የማኅበረሰብን ጤና፣ ደኅንነት እና ምቾት የሚያስጠብቅ መሆን ይኖርበታል። ማኅበራዊ ፕሮግራማችን ዜጎችን የሚያስተሣሥር፣ ከችግርና ከመከራ የሚታደጋቸው፣ የሀገርን አለኝታነት የሚያሠርጽ እና በሀገራችን አዎንታዊ ሰላምን የሚያረጋግጥ ይሆናል። ማኅበራዊ የልማት ፕሮግራማችን ኅብረ ብሔራዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብት እንዲሆን ዒላማ አድርጎ መንቀሳቀስ የፓርቲያችን የማኅበራዊ ፕሮግራም ዓላማ መገለጫ ይሆናል። ይህንንም እውን ለማድረግ በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን፣ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የከተማ ነዋሪ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የዜጎች አገራዊ አገልግሎት እንዲስፋፋ ፓርቲያችን ይሰራል።

የማኅበራዊ ፕሮግራም ግቦች

  1. ፍትሐዊነት፣ ጥራት እና አግባብነት ያለው የትምህርትና ስልጠና ስርዓት ማረጋገጥ
  2. መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ሥርዓት መዘርጋት
  3. የሀገራችንን ዐቅም ያገናዘበ የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓት መዘርጋት
  4. የሴቶችንና ወጣቶች የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጎልበት
  5. ብዝኃነታችንን ማዕከል ያደረግ የቋንቋ የባህልና ቅርስ ልማት