የኢኮኖሚ ፕሮግራም

የኢኮኖሚ ፕሮግራም ዓላማ፡- ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት

የብልጽግና ፓርቲ በኢኮኖሚ ፕሮግራሙ የሕዝባችን ሰፊ ክፍል የሆነውን አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ወጣት፣ ሴቶች እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች ማዕከል ያደረገ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት የሕዝባችንን የጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ዓላማ ይኖረዋል። ፓርቲያችን በሀገራችን ምርታማነትን እና ፍትሐገዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ወሳኝ አቅምና መሣሪያ ነው ብሎ ያምናል። በመሆኑም የመንግሥት በኢኮኖሚው ሥርዓት ውስጥ ያለው ተሳትፎ የገበያ መርሕን በመከተል ስትራቴጂካዊ በሆነ ሁኔታ ሀብት የሚፈጥር፣ በተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ማሕቀፍ ውስጥ የግሉን ዘርፍና ሌሎች የኢኮኖሚ ተዋናዮችን ተሳትፎ በማጎልበት ምርታማነትን በላቀ ደረጃና ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያሳድግ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህም መሠረት ፓርቲያችን ጥራት ያለውና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ሀገራችንን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማሸጋገር ያልማል።

የኢኮኖሚ ፕሮግራም ግቦች

  1. የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ መዋቅር መገንባት
  2. ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ልማት እና ምርታማነትን መሰረት ያደረገ ማኅበራዊ ፍትሕ ማረጋገጥ
  3. ሀብት ፈጠራን የሚያሳድግ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ መገንባት
  4. ከተሜነት እና የከተማ ልማትን ማስፋፋት